1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓመታዊው የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ጉባኤ በባኩ አዘርባጃን

ሸዋዬ ለገሠ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 3 2017

ዓመታዊው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ ማለትም COP 29 ትናንት ባኩ አዘርባጃን ላይ በይፋ ተጀምሯል። ከሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መጪው ሳምንት ዓርብ ድረስ የሚዘልቀው ጉባኤ ዋና ትኩረት ምን ይሆን?

COP 29  ጉባኤ
የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ COP 29 በባኩ አዘርባጃን ምስል Peter Dejong/AP/picture alliance

COP 29 በባኩ አዘርባጃን

This browser does not support the audio element.

«የምትሰሙት የሚቆጥር የሰዓት ድምፅ ነው። የዓለም የሙቀት መጠን ከ1,5 ዲግሪ ሴልሺየስ እንዳይበልጥ ለማድረግ ከመጨረሻው ገደብ ላይ ደርሰናል፤ እናም ጊዜ የለንም።»

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ለCOP 29 ጉባኤ ተሳታፊዎች ያስተላለፉት መልእክት ነው። በፍጻሜውስ ምን ይጠበቃል? ለጥቂት ደቂቃ አብረን እንቃኘው።

የዘንድሮው ጉባኤ ድባብ

የዘንድሮው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ተመሳሳይ ጉባኤዎች ጋር ሲነጻጸር ቀዝቀዝ ያለ ድባብ ይታይበታል። በበርካታ ሃገራት ከመጠን ያለፈ ኃይል ያላቸው የተፈጥሮ አደጋዎች ተከስተዋል። በአንድም በሌላም መልኩ በተፈጥሮ አደጋዎች ያልተጎበኘ ሀገር የለም። ባኩ አዘርባጃን ለሁለት ሳምንታት በሚካሄደው በዚህ ዓለም አቀፍ አሳሳቢ ርዕሰ ጉዳይ መነጋገሪያ በሆነት ጉባኤ ላይ ወደ 200 ሃገራት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከስፍራው የወጡ ዘገባዎች የሚያመለክቱት ግን በአብዛኛው በተለይም ግንባር ቀደም ሆነው ይመራሉ ከሚባሉ የየሃገራት መሪዎችና ወኪሎች ቁልፍ የሚባሉት አልተገኙም።

ከግንባት ቀደም ከባቢ አየር በካይ ሃገራት ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈው ሳምንት ባካሄደችው ምርጫ የፕሬዝደንትነት መንበሩ የአየር ንብረት ለውጥን በማይቀበሉት በቱጃሩ ዶናልድ ትራምፕ በመወሰዱ፤ ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ባይደን በዚህ ጉባኤ አልተገኙም። ከፈጣን የኢንዱስትሪ እድገቷ ጋር ተያይዞ ከዋናዎቹ ከባቢ አየር በካይ ሃገራት አንዷ የሆነችው ቻይና ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ ደግሞ ምክትላቸውን ወደ ጉባኤ ሲልኩ፤ የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዑርዙላ ፎንደር ላይንም እንዲሁ ብራስልስ ላይ ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት እንደማይገኙ ነው የተነገረው።

በዚህም ምክንያት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ በጉባኤው ላይ ተገኝተው ያስተላለፉት መልእክት ከወሳኞቹ ተዋንያን ጆሮ በቀጥታ እንዳልገባም ተጠቁሟል። ጉተሬሽ ግን ጠንካራ ትችት ያዘለ መልእክታቸውን ከማስተላለፍ አልተቆጠቡም።

«በዓለማችን ኤኮኖሚ በሁሉም ቦታ ያለው የዋጋ ንረት የአቅርቦቱን ሰንሰለት አናግቶታል። የምርቶች መቀነስ በየቦታው የምግብ ዋጋን ከፍ አድርጎታል። የቤቶች መውደም የመድህን ዋስትና ዋጋን በሁሉም ቦታ ጨምሮታል። ይህ ሊወገድ የሚችል የግፍ ታሪክ ነው። ሀብታሞች ችግሩን ያመጣሉ ድሆች ደግሞ ከፍተኛውን ዋጋ ይከፍላሉ።»

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽፎቶ ከማኅደርምስል Andrea Renault/AFP/Getty Images

የዘንድሮው ጉባኤ ትኩረት

ለከባቢ አየር ብክለት ታሪካዊ ሀላፊነት እንዳለባቸው የሚገለጸው በኢንዱስትሪ ያደጉት ሃገራት ለማዋጣት ቃል የገቡትና እስካሁን ፍንጩ ያልታየው ገንዘብ ጉዳይ በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የመንግሥታቱ ድርጅት የCOP 29 ዋነኛ መነጋገሪያ ነው። ከቅሪተ አጽም የሚገኘውን የነዳጅ ዘይት አጠቃቀም ለመቀነስ ብሎም ይህን ትቶ አስፈላጊውን የኃይል አቅርቦት ከታዳሽ እና ንጹሕ ምንጮች ብቻ ወደማድረግ ለመሸጋገር የሚደረገው ጥረትም የተወያዮቹን ጎራ ከፍሎ የሚያከራክር የሚያወዛግብ ካለፉት ተከታታይ ጉባኤዎች ሲመከርበት የቆየ በጥንቃቄ የሚታይ ጉዳይ ነው።

እንዲያም ሆኖ ወደ 200 ሃገራት ይሳተፉበታል ተብሎ ከተገመተው ከዚህ ጉባኤ መላው ዓለም ወደ ጽዱ የኃይል ምንጮች የሚያደርገውን ሽግግር ለመደገፍ በበርካታ መቶ ቢሊየኖች የሚቆጠር ዶላር ማሰባሰብ ታቅዷል። የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ስለመቀነስም እንደሚነጋገር ይጠበቃል። እንዲህ ያለው ሁሉንም የሚነካ ርዕሰ ጉዳይ ለውይይት በሚቀርበብ በዚህ መድረክ ውሳኔው ፖለቲካዊ ፍጥነት እንዲኖረው ለማድረግ ይችላሉ የሚባሉት ቁልፍ ተዋናዮች አለመገኘታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር  ኪር ስታርመር ይህ ዓለም አቀፍ ስብሰባና ውይይት ለሀገራቸው ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም የሚኖረውን ፋይዳ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል።  

«በእኔ ዕይታ ከፊታችን ሁለት መንገዶች አሉ፤ አንደኛው መንገድ፤ እርምጃ አለመውሰድና መዘግየት ለበለጠ ተጋላጭነት ይዳርጋሉ። ከ1,5 ዲግሪ በላይ የሚሆነው ሙቀት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በመቶዎችና ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለጎርፍና አደጋ፤ ለትልቅ የኤኮኖሚ አለመረጋጋትና ለብሔራዊ ዋስትና ማጣት ያጋልጣሉ። ሁለተኛው የምንጓዝበት መንገድ፤ ዓይናችንን በሰፊው ከፍተን የዛሬዎቹን ተግዳሮቶች ብቻ ሳይሆን የነገውንም ዕድሎች በጥብቅ መወሰን ነው። ይህ መንገድ ነው ወደ ብሔራዊ ደኅንነት፤ የኃይል አቅርቦት ነጻነት እና የሠራተኛውን ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ አስፈላጊውን የኤኮኖሚ መረጋጋት የሚያመራው።»

ስታርመር አያይዘውም ሀገራቸው በጎርጎሪዮሳዊው 2035 ታሳካዋለች ያሉትን የሙቀት አማቂ ጋዞች ቅነሳ ልኬት ይፋ አድርገዋል። 81 በመቶ። እንዴት ለሚለውም የንፁሕ የኃይል ምንጮች ተጠቃሚነቷን እንደምታስፋፋ ነው የጠቆሙት። በተቃራኒው የነዳጅ ዘይት አምራች ሃገራት ከቅሪተ አጽም የሚገኘውን የኃይል ምንጭ አጠቃቀም መቀነስ የሚለውን ሃሳብ ገና አልተቀበሉትም። የCOP 29 አስተናጋጅ ሀገር የአዘርባጃን ፕሬዝደንት ከዓለም የነዳጅ ዘይት ምርት 0,7 በመቶ ብቻ ድርሻ ያላት ሀገራቸው በሌሎች ልትተች አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል። ለአየር ብክለት 0,1 በመቶ አስተዋጽኦ የምታደርገው አዘርባጃንን የፔትሮል ሃገራት ከሚባሉትም መደመር አይኖርባትም ባይም ናቸው።

ጎርፍ ከባድ ጉዳት ያደረሰባት ስፔን ምስል JOSE JORDAN/AFP via Getty Images

የቀጠለው አሳሳቢው የተፈጥሮ አደጋ

ከሳምንታት በፊት በደረሰባት ከባድ የጎርፍ አደጋ ያላገገመችው ስፔን ፕሬዝደንት በጉባኤው ከተገኙ መሪዎች መካከል ናቸው። ምሥራቃዊ የስፔን ግዛቶችን አጥለቅልቆ በመኪና አውራ ጎዳናዎች ላይ ሳይቀር ሲገማሸር የታየው ከ200 በላይ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። የዘንድሮው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የአየር ጠባይ ሁኔታም ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ከፍተና ሙቀት የተመዘገበበት መሆኑን የዓለም ሜቴሪዎሎጂ ተቋም አስታውቋል። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ሴለስት ሳኡሎ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ፍጥነት ያሰጋል ነው ያሉት።

«የአየር ጠባይ ወቅታዊ መረጃ እንደሚያሳየው፤ 2024 በደረጃ ከተመዘገቡት ከፍተኛ ሙቀት የታየበት ዓመት ነው። ከ2023ም እንኳ የበለጠ ሞቃት ነበር፤ ከዚያ በፊት የተመዘገቡትን ከፍተኛ የተባሉትን ሁሉ በልጧል። ከ2015 እስከ 2024 ያሉት 10 ዓመታት በጣም ሞቃት መሆናቸው ተመዝግቧል። በአንድ ትውልድ ውስጥ ብቻ እንኳን የአየር ንብረት ለውጡ ፍጥነት አሳሳቢ ነው።»

የዓለም የሙቀት መጠን መጨመር ያስከተለው መዘዝ እየታየ በሚገኝበት ወቅት ትናንት በተጀመረው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ሃገራት የብክለት ቅነሳ እቅዳቸውን ማሳወቅ ጀምረዋል። በተመሳሳይ አንዳቸው ሌላቸውን የበለጠ ከባቢ አየርን በካይ አድርገው መተቻቸትም ታይቷል። በጉባኤው የተገኙት የአውሮጳ ኅብረት ተጠሪዎች በበካይነቱ ቻይና፤ ሳውድ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት እና ቀጠር ከኅብረቱ የማይተናነስ ሚና እንዳላቸው በማመልከት፤ የተጠቀሱት ሃገራትም የበኩላቸውን ተጨባጭ እርምጃ ለመውሰድ ወደድርድሩ በቁርጠኝነት እንዲመጡ ሲሉ ተደምጠዋል። ጉባኤው ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን እያነሳ እስከመጪው ዓርብ ይዘልቃል። በቀጣይ የጉባኤው አስተናጋጅ ሀገር ብራዚል መሆኗ ተጠቁሟል።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW