39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ተጠናቀቀ
ሰኞ፣ የካቲት 9 2018
39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ተጠናቀቀ
39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በአህጉሪቱ በቀጠሉ የፀጥታ ችግሮችና በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ውሳኔዎች በማሳለፍ ተጠናቋል። እ.አ.አ በ2030 ግጭቶችን በሙሉ ለማስቀም ያላቸውን ቁርጠኝነት መሪዎቹ በድጋሚ ማረጋገጣቸውን በጉባኤው ማጠቃለያ የወጣው መግለጫ አመልክቷል። የትግበራ እንጅ ውሳኔዎችን የማሳለፍ ችግር እንደሌለበት የሚገለጸው ሕብረቱ፣ ይሄንን ክፍተት ለመሙላት የደረሰበትን ውሳኔ አላብራራም።
ከየካቲት 7 ቀን 2018 ዓ/ም ጀሞሮ ለኹለት ቀናት በአዲስ አበባ የተካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ፣በተለያዩ የአህጉሪቱ አካባቢዎች ባሉ የፀጥታ ችግሮችና በሌሎችም አጀንዳዎች ላይ መግለጫ በማውጣት ትናንት የካቲት 8 ቀን 2018 ዓ/ም ተጠናቋል።
ጉባኤው ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የሠላምና ፀጥታ ምክር ቤት፣በአህጉሪቱ ባለው የሠላምና ፀጥታ ሁኔታ ላይ ያቀረበውን ሪፖርት ማዳመጡን መግለጫው አመልክቷል።
ይሄንን ሪፖርት መነሻ በማድረግም በአህጉሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የቀጠሉ ግጭቶች፣ ሽብርተኝነት፣ ኢሕገመንግስታዊ የኾኑ የመንግስት ለውጦች፣ አክራሪ ጽንፈኝነትና ሰብዓዊ ቀውሶች እጅጉን እንደሚያሳስቡት አስታውቋል ።እ.አ.አ በ2030 ግጭቶችን በሙሉ ለማስቀም ያላቸውን ቁርጠኝነት መሪዎቹ በድጋሚ ማረጋገጣቸውንም በጉባኤው ማጠቃለያ የወጣው ይሄው መግለጫ አመልክቷል። ኢሕገመንግስታዊ የኾኑ የመንግሥት ለውጦችን እንደማይታገሱም መሪዎቹ በዚሁ መግለጫ አስታውቀዋል።
በአህጉሪቱ ለቀጠሉ የጸጥታ ችግሮችእልባት ማስገኘት የተሳናቸውን የሕብረቱን የሠላምና ጸጥታ እንደዚሁም የአስተዳደር መዋቅሮች ለማሻሻል የቀረበውን ሪፖርት በተመለከተ ስለተደረሰበት ወሳኔ በግልጽ አልተብራራም። " ሕብረቱን ሰው ተኮር የኾነ፣የማስፈፀም ብቃት ያለው፣ተጠያቂነት ያለበትና አስተማማኝ የገንዘብ ምንጭ ያለው አድረጎ ለማጠንከር ጉባኤው ቀርጠኝነቱን አረጋግጧል" በማለት ብቻ ነው መግለጫው ያስቀመጠው።
የአፍሪካ ሕብረት በአህጉሪቱ ያሉ ችግሮችን ከመፍታት አንጻር ከፍተኛ ክፍተት እንዳለበት፣አብዛኞቹ ውሳኔዎቹም እንደማይተገበሩ የቅርብ ጊዜ ጥናት አመልክቷል። በእንግሊዝኛ ምህጻረ ቃል አይ.ኤስ.ኤስ በመባል የሚታወቀው የጸጥታ ጥናት ተቋም እ.አ.አ.በ2023 ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው፣የአፍሪካ ሕብረት የሠላምና ፀጥታ ምክር ቤት እ.አ.አ. ከ2004 ጀመሮ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች 90 በመቶው ተግባራዊ አልተደረጉም።
ሕብረቱ ግጭቶችን ለመፍታት ብቃትና የሠላም አቅድ ይጎድለዋል የሚል የጋዜጠኛ ጥያቄ የቀረበላቸው የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዮሰፍ፤ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጡም። "የግጭትና ያለመረጋጋት ሁኔታዎች ባለባቸው አካባቢዎች ሠላምና መረጋጋት ለማምጣት የምንጠቀምባቸው በርካታ ስልቶች አሉ" በማለት ብቻ ተናግረዋል ። አይ.ኤስ.ኤስ በመባል በሚታወቀው የጸጥታ ጥናት ተቋም ተመራማሪ የኾኑት ሙሳ ሶማሆህሮ፣ ሕብረቱ ግጭቶችን ከመፍታት አንጻርና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ የማይሆኑበት አንዱ ምክንያት፥ አህጉራዊው ተቋም የተዋቀረበት ሁኔታ መኾኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የመንግስታት ሕብረት መኾኑን ያስታወሱት ተመራማሪው፣አገራት ከህብረቱ ማዕቀፎችና ውሳኔዎች ጋር እንዲተባበሩ የሚያደርግ አሰገዳጅ ሁኔታ እንደሌለ አመልክተዋል።እናም የውሳኔዎች ተፈጻሚነት ፈተናዎች እንደሚገጥሙት አብራርተዋል። "የሉአላዊነት ጉዳይም አንዱ ፈተና ነው።የአፍሪካ ሕብረት የወሰናቸውን ውሳኔዎች በአባል አገራት ላይ መጫን አይችልም" በማለት አስረድተዋል። 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በሌላም በኩል በቅኝ አገዛዝና በባሪያ ንግድ ዘመን የተፈጸሙ ወንጀሎችን ስያሜ በተመለከተ መነጋገሩን ትናንት የወጣው መግለጫ አመልክቷል።
እስክንድር ፍሬው
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ