ኬንያና ደቡብ አፍሪቃ ከቪዛ ነፃ ስምምነት ተፈራረሙ
ቅዳሜ፣ ኅዳር 3 2015
ኬንያውያን ከመጪው 2023 የጎርጎሮሳዊው አዲስ ዓመት ጀምሮ፣ ያለቪዛ ደቡብ አፍሪቃ መግባት እንደሚችሉ መነገሩ ሰሞኑን ኬንያዉያን ያስደሰተ ዜና ሆኖ ሰንብቷል። ሁለቱ ሃገራት እዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት፤ የደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ በሳምንቱ መጀመርያ ላይ ኬንያ ናይሮቢን በጎበኙበት እና ከአዲሱ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ጋር የመግባብያ ሰነድ ከተፈራረሙ በኋላ ነዉ። የደቡብ አፍሪቃ እና የኬንያ ፕሬዝዳንቶችን፣ ሲያነጋግር የከረመዉ የደቡብ አፍሪቃ የነጻ መግቢያ ፈቃድ (ቪዛ) ጉዳይ በስምምነት ተፈቷል ሲሉ የሁለቱ ሃገራት ፕሬዚዳንቶች ከፊርማ ሥነ-ስርዓቱ በኃላ ንግግር አድርገዋል። የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የደቡብ አፍሪቃው አቻቸዉ ሲሪል ራማፎሳ፤ ናይሮቢ ላይ የተደረሰው ስምምነት ኬንያውያን ደቡብ አፍሪቃ ስለያዘችዉ የስደተኞች ፖሊሲ ላይ ለአስርት ዓመታት ሲሰነዝሩት የነበረውን ቅሬታ ሊያስቀር ይችላል ተብሎም ታምኖበታል። ይሁንና ኬንያዉያን በደቡብ አፍሪቃ ያለ ፈቃድ ከዘጠና ቀናት በላይ ቢቆዩ አልያም ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ቢገቡ ከባድ ቅጣት እንደሚከተላቸዉ ይፋ ሆንዋል። ደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ፤ ኬንያዉያንን ያለ ቪዛ ወደ ሃገራቸዉ እንዲገቡ የሚኒስቴር መስርያ ቤታቸዉ ስራዉን እያፋጠነ መሆኑን ገልፀዋል።
«ኬንያውያን ያለ ቪዛ ደቡብ አፍሪቃን መጎብኘት መቻል እንዳለባቸው፤ ይህም ከ ጥር 1 ቀን 2023 ዓ.ም እንደሚጀመርና ባለሥልጣኖቻችንም በተወሰነዉ ጊዜ ለመጀመር የሚያያካሂዱትን የሥራ ሂደት እንደሚያፋጥኑ ተስማምተናል።»
ኬንያዉያን ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለዓመታት ወደ ሲጓዙ ጥብቅ የቪዛ ደንብ በማሟላት ብቻ ነበር። በአዲሱ ስምምነት መሰረት፤ ኬንያዉያን በደቡብ አፍሪቃ፤ 90 ቀናት ለመቆየት፤ በመጀመርያ ደረጃ፤ የግብዣ ወረቀት፤ በሁለተኛ ደረጃ ደርሶ መልስ የአየር ትኬት፤ በሦስተኛ ደረጃ የቢጫ ወባ መከላከያ ክትባት ማረጋገጫ እና የኮሮና መከላከያ ክትባት ማረጋገጫ ማቅረብ ግድ ይላቸዋል። ያለ ግብዣ ወረቀት በቱሪስት ቪዛ የሚጓዙ ተጓዦች ደግሞ በደቡብ አፍሪቃ ለሚቆዩበት ቀናት በቂ የኪስ ገንዘብ እና የመኖርያ ቦታ እንዳላቸዉ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ናይሮቢ ላይ ከተካሄደዉ የስምምነት ፊርማ ስነ ስርዓት በኋላ የኬንያዉ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ የደቡብ አፍሪቃ አቻቸዉን አመስግነዋል።
«የኬንያን ህዝብ ወክዬ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየውን በኬንያ እና በደቡብ አፍሪቃ መካከል ከቪዛ ነጻ ጉዞን ለማሳካት ስለተካሄደዉ ሥራ ኬንያ ያላትን አድናቆት እገልጻለሁ። ክቡርነቶ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ በግል ጣልቃ በመግባቶ እና ባለሥልጣናቱ ለተሳተፉበት ያካበተ የሥራ ልምድ ምስጋና ይድረሶት »
በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በሚገኘዉ በኪሊማኒ አስጎብኝ ድርጅት ዉስጥ የሚሰራዉ ቲሞቲ ኦቲኖ እንደሚለዉ የደቡብ አፍሪቃ የነጻ ቪዛ ስምምነት ቢያስደስተዉም፤ ደቡብ አፍሪቃ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ዓመታት ስለፈጀባት ትንሽ ቅሬታ እንዳለዉ ተናግሯል።
«ደቡብ አፍሪቃ ከአውሮጳ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለሚጓዙ 28 ሀገሮች ያለ ቪዛ በነፃ ታስገባለች። ከኛ ከአፍሪቃ ወደ አሜሪካ የሚሄዱ 15 ሀገሮች ብቻ ናቸዉ ያለ ቪዛ መግባት የሚችሉት። ጥናቱን የተመለከትን እንደሆነ አንድ አፍሪቃዊ በሌላዉ ክፍለ ዓለም የሚያጋጥመዉ እንደዚህ ያለ ነገር ነዉ። ይህን በእናት አገርህ ላይ ሲደረግ በተወሰነ መጠን ንቀት ነዉ። ይጎዳል።»
በደቡብ አፍሪቃ በህገ ወጥ መንገድ የገባ አልያም ከ 90 ቀናት በላይ የቆየ ኬንያዊ በናይሮቢዉ መንግሥት ወጪ ወደ ሃገሩ ይጠረዛል። ፕሬዝዳንት ራማፎዛ ኬንያውያን ያለ ትራንዚት ቪዛ በደቡብ አፍሪቃ አየር ማረፊያዎች እንዲሸጋገሩም ፈቅደዋል። ይሁንና ተጓዞቹ፤ በነጻዉ ፈቃድ መቆየት የሚችሉት ኤርፖርት ዉስጥ ብቻ ይሆናል። ቀደም ሲል ሃገሪቱ ለትራንዚት ተጓዞች ኬንያዉያን ቪዛን ትጠይቅ ነበር።
የደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዚዳንት እና የኬንያ አቻቸዉ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ከነፃ የመግብያ ፈቃድ ቪዛ በተጨማሪ በሁለቱ ሐገራት የንግድ፣ እና የአህጉሪቱን ብሎም የአካባቢያቸዉን ቀጠና ደህንነት በተመለከተ የመግባብያ ሰነድ ተፈራርመዋል። ስምምነቱ ከምስራቅ አፍሪቃ በኢኮኖሚ ቀደምት የሆበችዉን የኬንያ እና የደቡብ አፍሪቃን የግንኙነት ይጠናከራል ሲሉ የደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዚዳንት፤ ተናግረዋል።
«ኬንያ በምስራቅ አፍሪቃ በምጣኔ ሃብት ግንባር ቀደም ሃገር ናት። ደቡብ አፍሪቃም በደቡባዊ አፍሪቃ ሃገራት በኢኮኖሚ ቀዳሚዋ ሃገር ናት። ስለዚህም የንግድ መጠኑን በዘላቂነት ለማሳደግ እና አንዳችን በሌላው ኢኮኖሚ ላይ የበለጠ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ጠንካራ ቁርጠኝነት መኖሩን አሳይተናል።»
ራማፎዛ ሁለቱ ሃገራት የአፍሪቃን ችግር በአፍሪቃዊ መፍትሄዎች ለመፍታት አህጉሪቱን እንደሚያበረታቱም ገልፀዋል።
« ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢያችንና በአህጉራችን ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ለማድረግ እንዲሁም በምናደርጋቸው ሌሎች ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች ትኩረታችን እንዳይከፋፈል ተስማምተናል ። ለአፍሪቃ ችግሮች የአፍሪቃ መፍትሄዎችን እናበረታታለን።»
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ