ለሰሞኑ ጥቃት የቀጠለው የፍትሕ ጥሪ፤ የመንግሥትና መገናኛ ዐዉታሮች ምላሽ
ዓርብ፣ ጥቅምት 20 2019
ለሰሞኑ ጥቃት የቀጠለው የፍትሕ ጥሪ፤ የመንግሥትና መገናኛ ዐዉታሮች ምላሽ
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አርሲ ውስጥ ለተፈፀመው ግድያ ፍትሕ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማሕበረ ቅዱሳን ጠየቀ። ማሕበሩ በኢትዮጵያ ሕዝብ ግብር የሚተዳደሩ ያላቸው መገናኛ ዐውታሮች በተደጋጋሚ ተፈጽሟል ያለውን ጥቃት እንዳልሰሙ ማለፋቸውን አጥብቆ አውግዟል። የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች እና ይመለከተናል ያሉ ኹሉ ግድያውን በማውገዝ ድርጊቱ እንዲቆም ተጠያቂነትም እንዲኖር እየጠየቁ ነው። ይህ የወንጀል ድርጊት መከሰቱ ብርቱ መነጋገሪያ ጉዳይ ቢሆንም የፌዴራል መንግሥትም ሆነ "የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን" እስካሁን ምንም ያሉት ነገር የለም። በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡ ሁለት ሰዎች እንዲህ ያለው ዝምታ "አደገኛ" እና ሰዎች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲገቡ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ የመንግሥት እና የመገናኛ ዐውታሮች ዝምታ ምን ትርጉም አለው?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መስከረም 10 እና 14 ቀን 2019 በኦሮሚያ ክልል አርሲ ውስጥ "ግፍን በተሞላ ጭካኔ" ባለችው ኹኔታ 60 ምዕመናን መገደላቸውን መግለጿን ተከትሎ፣ አንድም ይህ ለዓመታት የተደጋገመ ጥቃት የሚቆመው መቼ ነው? በሚል ከተለያየ አቅጣጫ የበረታ ሀዘን እና የሥጋት ጥያቄ ፈጥሯል። በሌላ በኩል የፌዴራሉ መንግሥት እና ከሕዝብ በሚሠበሰብ ግብር የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ዐውታሮች፣ ለእንዲህ ያለው አንገብጋቢ ጉዳዩ የሚያሳዩት ቸልታ ወይም ባላየ የማለፍን አዝማሚያ ብዙዎች አሳሳቢነቱ እያደገ የመጣ ሌላ አደጋ አድርገው እየገለፁት ነው። "መንግሥት እና በሕዝብ ግብር የሚተዳደሩ ሚዲያ [ዎች] እንዲህ አይነት ጭፍጨፋዎችን ባላዬ ባልሰማ ዝም ካሉ የዚያ ወንጀል ተባባሪ ወይም ደግሞ በወንጀሉ ላይ እንደመስማማት ነው ሊቆጠር የሚችለው።"
ማሕበረ ቅዱሳን ያቀረበው የፍትሕና የተጠያቂነት ጥሪ
ማሕበረ ቅዱሳን "ጭፍጨፋ ይቁም፣ እውነት ፍትሕ እና ተጠያቂነት ይስፈን" ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ ድርጊቱን ተከትሎ "በሥጋት ውስጥ ሆነው እና ተፈናቅለው ላሉት ሕጋዊ ከለላ እንዲሰጥ፣ ከሞት የተረፉት በአስቸካይ ወደ መኖሪያ ቦታቸው እንዲመለሱ፣ ነጻና ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ፣ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እና ጥፋተኞችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል። ይህ ጥያቄ የብዙ ዜጎች ጭምር ነው። አንዱ ክስተት ታልፎ ሌላው መፍትሔ ሳያገኝ በተመሳሳይ ቦታና ኹኔታ መቀጠሉ ግን በሕዝብ ዘንድ ነገም ላለመደገሙ ዋስትና የለም የሚል እያደገ የመጣ ሥጋት እየፈጠረ ይገኛል።
እንዲህ ያለው የተደጋገመ ችግር በሂደት የሚኖረው ውጤት ምንድን ነው?
በኦሮሚያ ክልል አርሲ እና ወለጋ አካባቢዎች ሕፃናትን፣ ሴቶችን እና አረጋዊያንን ጨምሮ ምንም የትጥቅ እንቅስቃሴ ውስጥ የሌሉ ሰዎችን በማንነትና በሃይማኖት ለይቶ ማጥቃት ለዓመታት ተደጋግሟል። ይህ በማኅበራዊ ግንኙነትም ይሁን በሰብአዊ መብት ጥበቃ ረገድ የሚኖረው ተጽዕኖ ምንድን ነው? በሚለው ላይ ስለ ሰዎች መብት በመሟገት የሚታወቁትን አቶ ያሬድ ኃይለማርያምን ዛሬ ጠይቀናቸዋል።
"ማኅበረሰቡ መንግሥት ለተበደሉ ሰዎች የማያዝን፣ ለዜጎች ጥበቃ የማያደርግ፣ ዜጎች በማንም ጥቃት እንዳይፈፀምባቸው የማይከላከል፣ አጥፊዎችንም የማይቀጣ ነው ብለው በመንግሥታቸውም፣ በሀገራቸውም ተስፋ እንዲቆርጡ እና ጨለምተኛ አስተሳሰብ በሀገሪቱ ውስጥ እንዲስፋፋ ያደርጋል።" እንዲህ ያለው ተከታታይነት ያለው ግድያ፣ ማሰቃየት፣ ንብረትን የማውደምና ያንንም በምስል እየቀረፁ የማስተላለፍ ወንጀል በተለይ በመንግሥት በኩል የሚሰጠው አናሳ ትኩረት በአቶ ያሬድ ምልከታ ሰዎች ወደ ኃይል አማራጭ እንዲያማትሩ እና ፍትሕንም በራስ ወደ ማፈላለግ አቅጣጫ እንዲገፉ ያደርጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ምክትላቸዉ ዛሬ አርብ ምን አሉ ?
የኢትዮጵያ መንግሥት የንፁሃን ዜጎችን ግድያ እንዲያስቆም፣ ፍትሕና ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች በተደጋጋሚ እየተጠየቀ ይገኛል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች "ዛሬ የመጀመሪያዎቹ 26 የከተማ አውቶብሶች ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ ተለውጠው ሥራ ላይ በመዋላቸው የተሰማኝን ደስታ መግለጽ እፈልጋለሁ።" ብለዋል። ዐቢይ ስለ አርሲው ግድያም ሆነ በሞያሌ ከ 50 ሺህ በላይ ሰዎችን ስላፈናቀለው አዲስ ቀውስ ግን እሳቸውም ሆነ የሕዝብ የሚባሉት መገናኛ ብዙኃን ምንም ያሉት ነገር የለም። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህም "በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በበደኖ እና በደደር ወረዳ በክላስተር የለማ የስንዴ ሰብል።" የሚል የግብርና ልማት ምስሎችን ከማጋራት ውጪ ስለዚህ ብዙ ውግዘት እና ሀዘን ስለፈጠረው ወቅታዊ ጉዳዩ ምንም ከማለት ተቆጥበዋል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ