1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በምዕራብ ሸዋ ዞን ጨሊያ ወረዳ የበረታው “የሽፍቶች” ጥቃት

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ ሐምሌ 11 2017

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጨሊያ ወረዳ ሶኮሩ ቀበሌ ታጥቀው በአከባቢው ዝርፊያን የሚፈጽሙ “ሽፍቶች” እየገደሉ መሆኑንም የአከባቢው ማህበረሰቦች እና የጭነት አሽከርካሪዎች አማረሩ፡፡ የአከባቢው ነዋሪዎችም ሆነ በዚያ ለሚያልፉ ሁሉ ፈታኝ ነው የተባለው ይህ አከባቢ ላይ የሚፈጸመዉ ወንጀል እልባት ሊበጅለት ይገባል ብለዋል።

ምዕራብ ሸዋ ዞን
ምዕራብ ሸዋ ዞን ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በምዕራብ ሸዋ ዞን ጨሊያ ወረዳ የበረታው “የሽፍቶች” ጥቃት

This browser does not support the audio element.

በምዕራብ ሸዋ ዞን ጨሊያ ወረዳ የበረታው “የሽፍቶች” ጥቃት


በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጨሊያ ወረዳ ሶኮሩ ቀበሌ ታጥቀው በአከባቢው ዝርፊያን የሚፈጽሙ “ሽፍቶች” እየገደሉ መሆኑንም የአከባቢው ማህበረሰቦች እና የጭነት አሽከርካሪዎች አማረሩ፡፡ ከሰሞኑ “ሽፍቶቹ” ተከታትለው በአከባቢው እያለፉ ከነበሩ አራት ተሽከርካሪዎች መካከል የሁለቱን አሽከርካሪ ሹፌሮች ገድለው ሌሎቹን ደግሞ በማገት ለማስለቀቅያ እስከ 300 ሺህ ብር እንደከፈሉ የተጎጂ ቤተሰቦች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን በጨሊያ ወረዳ ሶኮሩ ቀበሌ “በሽፍቶች” ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው አስተያየት ሰጪዎች ለዘመናት የአከባቢው ነዋሪዎችም ሆነ በዚያ ለሚያልፉ ሁሉ ፈታኝ ነው የተባለው ይህ አከባቢ ላይ የሚፈጸመዉ ወንጀል እልባት ሊበጅለት ይገባል ብለዋል። 

የእገታ እና የዉንበዳ ወንጀሎች መበራከት
አደገኛዋ ስፍራ ጎብን-ጌዶ


ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ጠዋት 2፡30 ግድም ከሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ጅማ ራሬ ወረዳ ጎበን ከተማ ማልደው ወደ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጌዶ አቅጣጫ አብሮ ለመጓዝ የተነሱ የአራት የጭነት ተሽከርካሪ ሾፌሮች የአደጋው ሰለባዎች ናቸው፡፡ ተጠባብቀው አብሮ ለመነሳታቸውም ዋናው ምክንያት ደግሞ ከጎበን-ጌዶ የሚወስደው መንገድ የተቆፋፈሬና ምቹ አለመሆኑና በአከባቢው የሚያሰጋው የጸጥታ ችግር ነው፡፡
“ጎበን ከታለፈ ትልቅ ስጋት ነው ያለው” የሚሉት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የተጎጂ ቤተሰቦች እንደተሰጋም አልቀረ አራቱ ሾፌሮች 30 ደቂቃ ግድም እንደተጓዙ የተኩስ እሩምታ ይከፈትባቸዋል፡፡ ከተጎደሉ ሾፌሮች አንዱ የሆነው የጃምቦ ግርባ ወንድም ፈልመታ ግርማ የወንድማቸውና ጓደኞቹን ጥቃት እንዲህ አስረድተዋል፡፡ “ከፊትለፊት ስጓዝ የነበረው ቶማስ ረታ የተባለ ሾፌር መሪው ላይ ነው ተመቶ የተገደለው። በሩንም አልከፈተም፡፡ ወንድሜ ጃምቦ ግን ምንድነው የተፈጠረው ብሎ ረዳቱንና አጠገቡ የጫናቸውን ሰዎች አረጋግቶ ከመኪናው በመውረድ የኋላ ጎማ ተመቶ እንደሆን ለማየት ዞር ሲል ነው የተኩስ እሩም ከፍተውበት እዚያው ጎማ ስር የወደቀው፡፡ ከቶማስ ቀጥሎ ሁለተኛ ላይ የነበረው ሾፌር ነገሩን አይቶ ስሸሽ የባህር ዛፍ ጫካ ውስጥ ገብቶ በአጋጆች እጅ በመውደቁ እሱን ሁለት ቀን አሳድረውት 300 ሺህ ብር አስከፍለው ለቀቁት፡፡ ሌላኛው ሾፌር ትንሽ ቆስሎ ከሌሎች ረዳቶች እና ተሳፍረው ከነበሩ ሰዎች ጋር አመለጡ” ብለዋል፡፡አደገኛዉ የአዲስ አበባ-ሰላሌ-ጎጃም መንገድ


የከባድ መኪና ሾፌር ላይ ያነጣጠረው ጥቃት


በዚህ አከባቢ እስካሁን የተለመደው ሾፌሮችን በተለይም የጭነት አሽከርካሪዎችን በማገት ገንዘብ መቀበል ነበር ያሉት የተጎጂው ቤተሰብ አስተያየት ሰጪ፤ እንዲህ ያለ የነፍስ ማጥፋት ጥቃት ያልተለመደ እንግዳ ነገር ነው ብለዋል፡፡ ስለ እነዚህ አጋቾች ማንነትም የተጠየቁት አስተያየት ሰጪው፤ “እነዚህ እንኳ ለፖለቲካ ፍላጎት የተደራጁ ታጣቂዎች ሳይሆኑ ለዝርፊያ የተደራጁ ሽፍቶች ናቸው፡፡ ቁጥራቸውም ውስን ሲሆን በዝርፊያ ላይ ነው የተሰማሩት፡፡ ይህ ጎበን የሚባል አከባቢ ከደርግ ጊዜም ጀምሮ ጥንትም በዚህ ነው የሚታወቀው፡፡ ባለፉት ስድስት ሰባት ዓመታት የመንግስት ታጣቂዎች እና በጫካ መንግስትን የሚወጉ አካላት በስፋት ይንቀሳቀሱበት ስለነበር ሽፍቶቹ ጠፍተው ነበር፡፡ አሁን ግን በዚህ ዓመት ባሰባቸው፡፡ አሁን በክረምት ወቅት ደግሞ አከባቢው በጉም ስለሚሸፈን በሩቅ አይቶ ማምለጥ እንኳ ስለማይቻል ስጋቱ ከፍቷልም” ነው ያሉት፡፡
የአንደኛው የሟች ሾፌር የቶማስ አባት አቶ ረታ በበኩላቸው በሰጡን አስተያየት፤ “ልጄ እንደማንኛውም ሰው ለስራ ነበር የወጣው፡፡ በዚያ ቦታ ከጎበን ጅምሮ እስከ ቴሌ ከጌዶ በታች ሁሌም የማይጠፉ ሌቦች አሉ፡፡ ልጄ እህል ጭኖ እየመጣ ነበር፡፡ ድሮ የምናውቀው አግተው ገንዘብ ነበር የሚቀበሉት፡፡ ይህን ደግሞ እንኳ ግለሰብ መንግስትም ያውቀዋል፡፡ አሁን ግን ልጄ ላይ ከመተኮስ በቀር የጠየቁት ነገር የለም፡፡ በዚያው ከመኪናው ሳይወርድ መቱት ሞተ” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ብዙ ሾፌሮች በዚያ ስያልፉ ገንዘብ ከፍለው ህይወታቸውን አትርፈዋል ያሉት የተጎጂው አባት “ልጄ አገሬ ነው ብሎ በቆሎ እንጂ ኮንትሮባንድ አልጫነም” በማለት ሞት የማይገባው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “እኔ አሁን ልጄን ከምገድሉብኝ ሚሊየንም ብጠይቁኝ ንኑን መኪና ሽጬ ብሰጥ ነበር ምመርጠው” በማለት ቁጭታቸውንም ገልጸው በተለይም እህል ጭነው በዚያ የሚልፉ አሽከርካሪዎች በውንብድና ላይ የተሰማሩት የነዚህ ሽፍቶች ሰለባ እንደሚሆኑም አስረድተዋል፡፡በምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ 19 የመንግስ ታጣቂዎች መገደላቸውን

ምዕራብ ሸዋ ዞን ምስል፦ Seyoum Getu/DW


የቀረበው የመንግስት ትኩረት ጥሪ
ነገሩ ዓመታትን ካስቆጠረና ሰርቶ የሚተዳደረውን ማህበረሰቡን በዚህ ልክ ካስመረረ ለምን ይሆን ትኩረት ያጣው በሚልም የተጠየቁት ተጎጂ አባት መንግስትን ወቅሰዋል፡፡ “እኛ ሌሊት ተነስተን የመረጥነው መንግስት እንደ መንግስት ድርሻውን እንዲወጣ ነው፡፡ እንዲያስተዳድረን አይደለምን፤ እኔ አሁን ልጄን አጥቻለሁ እንደፈለኩ ብናገር ማን ልፈርድብኝ” በማለት መንግስት ጉዳዩን እያወቀ ለምን ዝም አለ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ልጃቸውን ጨምሮ በጥቃቱ የተጎዱት ሾፌሮች ሰኔ 25 ቀን 2017 ጠዋት 2፡30 ግድም በይፋ ሲዘረፉና ስገደሉ መንግስት እየተመለከተ ዝም ከማለት ይልቅ ከጥንትም የዘለቀውን ውንብድና እልባት ብሰጥ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ ግን የሞተ ሰው የለም በማለት ማብራሪያውን ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ “የሞተ ሰው የለም፡፡ ከየት አመጣሆ ማንም አልሞተም” በማለት ነው ስልካቸውን የዘጉት፡፡ የተጎጂ ቤተሰቦቹ ግን ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ረፋዱን 4፡00 ሰዓት ግድም ጎበን በሚባለው ስፍራ የነበረው የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ደርሰው የሟቾችን አስክሬን አንስተው መቅበራቸውን አመልክተዋል።


ሥዩም ጌቱ 
አዜብ ታደሰ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW