በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የሰሜን ኢትዮጵያ ጉብኝቶች
ዓርብ፣ ሐምሌ 10 2018
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የሰሜን ኢትዮጵያ ጉብኝቶች
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ባለፈው ሳምንት መቀሌን፣ በዚህኛው ደግሞ ጎንደርን ጎብኝተዋል። አምባሳደሩ ሀገራቸው በትግራይ ክልል ለሰላም፣ ለመረጋጋት እና ለሰብአዊ ማገገም ያላትን ቁርጠኝነት ለማረጋገጥ መቀሌ መጓዛቸው ሲነገር፣ ጎንደር ላይ ደግሞ ስለ ሰላም ተስፋዎች እና ለኢትዮጵያ እና አሜሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት ስለሚኖሩ ዕድሎች ስለመምከራቸው ተገልጿል።ይህ የአምባሳደሩ የሰሜን ኢትዮጵያ ከተሞች ጉብኝት፣ የፌዴራል መንግሥት እና ህወሓት ውዝግብ ዳግም ባየለበት፣ አዲስ አበባ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤን በምታስተናግድበት ወቅት ነው። በጉብኝቱ አላማ አንደምታ ላይ ሀሳባቸውን የጠየቅናቸው አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኝ፣ ነገሩን ከፌዴራል መንግሥት እና ህወሓት ፍጥጫ እንዲሁም ከቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት አንጻር ተመልክተውታል። በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ትናንት ወደ ጎንደር ከተማ ተጉዘው ከአካባቢው እና ከክልል ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን ኤምባሲያቸው ገልጧል። አምባሳደሩ ስለ ሰላም ተስፋዎች እንዲሁም ለአሜሪካ እና ኢትዮጵያ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ስለሚያመጡ ዕድሎች መነጋገራቸው ተጠቅሷል።
በዚህ ጉዳይ ተንታኞች ምን ይላሉ?
የአምባሳደሩጉብኝት ፖለቲካዊ መልኩ ጉልህ መሆኑን የሚጠቅሱ ተንታኞች፣ ዋሽንግተን መቐሌን እና ጎንደርን በመጎብኘት ዘላቂ ሰላም፣ የፖለቲካውይይት እና የኢኮኖሚ ማገገም እርስ በርስ የተሳሰሩ መሆናቸውን እያመለከተች ስለመሆኑ ይጠቁማሉ። ጉብኝቱን የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የሚደረግ ጥረት አካል ከመሆኑም በላይ ዩናይትድ ስቴትስ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ የበለጠ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደት እና የረጅም ጊዜ መረጋጋት እንዲኖር እንደምትደግፍ ለማሳየት የሚደረግ ጥረት አካል አድርገውም ይተረጉሙታል።
በጉብኝቱ ላይ ያላቸውን ምልከታ ያጋሩን አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ከመሰል ጉብኝቶች በኋላ ኤምባሲዎች የሚያወጧቸው መግለጫዎች "ጠቅላላ ታሪኩን" ባይገልፁም በተለይ የመቀሌው ጉዞ አሜሪካ የፕሪቶርያ ስምምነት ዋና ተዋናይ እንደመሆኗ አፈጻፀሙ ላይ ችግሮች ሲከሰቱ "ዝም ማለቷ በተዓማኒነቷ ላይ እንዲሁም በቀጣይ ልታሸማግላቸው በምትችላቸው ጉዳዮች ላይ ጥላ ሥለሚያጠላ ያንን ለማስቀረት የተደረገ" ጉብኝት አድርገው ገልፀውታል። "የህወሓት እና የፌዴራል መንግሥቱ ጉዳይ ተካሮ በሚገኝበት ኹኔታ የአሜሪካው አምባሳደር ማሲንጋ ወደ ትግራይ መሄዳቸው ለእኔ ምሳሌያዊ ከመሆን ያለፈ ተጨባጭ ጦርነትን ሊያስቀር የሚችል ውጤት ይኖረዋል ብየ አልገመግምም።"
የጎንደር ከተማ ከንቲባ ከአምባሳደሩ ጋር ስለተነጋገሩባቸው ጭብጦች ምን አሉ?
የጎንደር ከተማ ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ከአምባሳደሩ ጋር በምን በምን ጉዳዮች ላይ እንደመከሩ ለመጠየቅ በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም "ውጤታማ እና ስትራቴጂካዊ" ያሉትን "የሁለትዮሽ ውይይቶችን" ማድረጋቸውን በማኅበራዊ መገናኛ ዐውታሮች በተለቀቀ ጽሑፍ ጠቅሰዋል። ከንቲባው "በቅርስ ጥበቃ፣ በዘላቂ የባህል ቱሪዝም ልማት፣ ኃላፊነት በሚሰማው የግል ኢንቨስትመንት እና ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች በሥራ ፈጠራ ላይ ድጋፍ በማድረግ አጋርነታችንን ለማስፋት ጥሪ አቅርበናል" ብለዋል።
አክለውም የፕሪቶሪያው ስምምነት አከራካሪ ስለሚለው አንደኛው አካባቢ "የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አሁን የራሱን አካባቢ እያስተዳደረ መሆኑ የታሪካዊ እና የአስተዳደር ማንነታቸው ትክክለኛ እና ሕጋዊ መልሶ ማቋቋም መሆኑን በይፋ ገልጸናል።" ብለዋል። ተንታኙ እንደሚሉት ግን አሜሪካ በአምባሳደሯ በኩል በሳምንት ውስጥ ሁለቱም ቦታዎች መገኘቷ "ሁለቱም ቀጣና ላይ ሄደዋል የሚል" ድምፅ ከማሰማት የዘለለ አይሆንም።
"በዲፕሎማሲዋ በኩል አንደኛው የተንጋደደ እንዳይሆን ሁለቱም ቀጣና ላይ ሄደዋል የሚል ድምፅን ለማሰማት ካልሆነ በቀር በቂ ትኩረት ሰጥተው በሚገባው የክብደት ደረጃ [አማራ ክልል ያለውን ጦርነት] እየተንቀስልቀሱ ነው የሚል አረዳድ የለኝም።" የጎንደር ከተማ ከንቲባ እንዳሉት አምባሳደር ማሲንጋ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት "በሕዝብ ጤና፣ በትምህርት እና በባህላዊ ቅርስ ጥበቃ ዘርፍ ያለውን ዘርፈ ብዙ አጋርነት ለማስፋት እና ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።" ብለው ጽፈዋል።
የቀጣናዊ ጉዳይ መልክ የያዘው የአካባቢው ኹኔታ
ይህ የአምባሳደሩ የሰሜን ኢትዮጵያ ከተሞች ጉብኝት፣ የፌዴራል መንግሥት እና ህወሓት ውዝግብ ዳግም ባየለበት፣ በሌላ በኩል አዲስ አበባ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤን በምታስተናግድበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት "ፅምዶ" የተባለ ጥምረት እንደተነሳበት ደጋግሞ በሚገልፅበት ማግሥት የተደረገም ነው። ለዲፕሎማሲ ተንታኙ ግን ይህ የሱዳን እና የኤርትራ መንግሥታት ብሎም የህወሓት እና የፋኖ ጥምረትን የሚያሳይ "ተጨባጭ" ማስረጃ የለም። "የፌዴራል ማንግሥቱ በጣም ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ጉዳዩን [ከህወሓት ያለውን ውዝግብ] ቀጣናዊ ነው የሚል አንደምታ እንዲኖረው አበክሮ እየሠራ ይመስለኛል።"
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ