በአፋር እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት የሰዎች ህይወት አለፈ
ሰኞ፣ ጥቅምት 16 2019
በአፋር እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት የሰዎች ህይወት አለፈ
በነፍስ ወከፍ መሳሪያ ታጅቦ በተደጋጋሚ የሚነሳው ይህ ግጭት ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ የ200 በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። በ2017 ዓ.ም በሁለቱ ብሄሮች መካከል የተደረገውን የእርቅ ስምምነት የሚያስፈጽም የመንግስት የጸጥታ አካል ባለመኖሩ እና ችግሩ በቸልተኝነት በመታየቱ ግጭቱ ሊቆም እንዳልቻለ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የአገር ሽማግሌዎች ገልጸዋል።
በአፋር ክልልጭፍራ እና እዋ ወረዳዎች በአማራ ክልልሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ አዋሳኝ ስፍራዎች ላይ ቅዳሜ ጥቅምት 14 ቀን 2019 ዓ/ም በተቀሰቀሰ ግጭት የሶስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሌሎች ሶስት ሰዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ተናገሩ። ግጭቱ በነፍስ ወከፍ መሳሪያ የታጀበ መሆኑን የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች ከባለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በተደጋጋሚ መከሰቱን ነው የሚናገሩት።
"አሁን ግጭት የሚነሳበት በጃራ ካምፕ ቀጠና ያለው እና ቀበነዋ እና እዋ የሚዋሰኑበት ማለት ነው። ከእኛ በኩል ሁለቱም ሀብሩ ወረዳ ናቸው። ከታች በኩል ደግሞ የጭፍራ ወረዳ እና እዋ ወረዳ ናቸው። ባለፈው ከእኛ በኩል ሶስት ተመተዋል። ሁለት የሞተ አንድ የቆሰለ ከታች በኩል ደግሞ ሶስት ተመተዋል። አንድ የሞተ አንድ ከባድ ቁስል አንድ ቀላል ቁስል ከታች አጠቃላይ ስድስት ህይወት ማለት ነው። "
ባለፉት 10 ዓመታት በአካባቢው የሚታየውን የእርስ በርስ ግጭት ለማስቆም በ2017 ሁሉንም ያካተተ እርቅ ቢፈጸምም አተገባበሩ የአካባቢው የጸጥታ አካላት ድጋፍ ስለሌለው ዳግም ግጭት መከሰቱ ነው የወጣት ሙሳ ሰይድ የሚገልጸው። "ህጎች ወጥተው ነበረ። በሰዓቱ ሀራ ላይ በተደረገው እርቅ ። እነዚህን ህጎች የሚያስፈጽም አካል ባለማግኘቱ ግጭቱ ቀጥሏል። ማለት ከእኛ አቅም በላይ እኛ እጃችን ላይ ፖሊስ የለንም፣ ባጀትት የለንም፣ ምን የለንም። ዝም ብሎ የተዋቀረ ወጣት ብቻ ነው በጎ ፈቃደኛ።"
ግጭቱን የአጠቃላይ የማህበረሰቡ ለማድረግ የሚጥሩ አካላት አሉ የሚሉት አስተያየት ሰጪም በቂ ትኩረት ለችግሩ ባለመሰጠቱ ጉዳዩ የማይመለከታቸውን ንጹሃን ጭምር እየሞቱ ነው ይላሉ። "አንዳንዶ ተንኮለኛ መሀከላቸዉ ተንኮስ አድርጐ ይሄዳል። ከዛ በኋላ ወረራ ይሆንና። ወደነበረው እንደገና መልሶ ወደ ግጭት። የብሄር ጦርነት የማስመስለር ይሞክራሉ። በቃ እንጨት ለቀማ ስሄዱ እዛው ይሞታሉ በዛ በኩል ያሉት በዚህ በኩል ደግሞ እንስሳት ቦታ ላይ ነዉ የሚገናኙት በተገናኙ ሰአት በቃ ተደባብተው ነው የሚገደሉት።"
ባለፉት 10 ዓመታት ትኩረት የተነፈገው የሁለቱ አዋሳኝ አካባቢዎች የማህበረሰብ ግጭት ከ200 በላይ ሰዎች መሞት ምክንያት መሆኑን የአፋር አማራ ማህበረሰብ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ይማም ጉርሻ ይገልጻሉ። "አሁን አሁን ካስታረቅነው ወዲህ የሞተው ሳይጨምር ሁለት መቶም ናምን ሞተዋል። በዚህ በአስር ዓመት ውስጥ በስምንት ዓመት ውስጥ። በጣም አሁን እንግዲህ በየሳምንቱ በየቀኑ እንደዚህ እንደዚህ የሚቀጠፉ አሉ። ግን ፖለቲካው እንትን ስላላደለ አሁን ይሄ ጉዳይ ፖለቲካውን ስለማይነካ የከብት እረኞች ነው ምንድነው እየተባለ ነው በቸልተኝነት የሚተላለፈው ግን ግጭቱ በጣም እየሰፋ ነው። "
በተደጋጋሚ በሁለቱ ብሄሮች መካከል የሚነሱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፈታት ደም ማድረቅ ያስፈልጋል የሚሉት የሀገር ሽማግሌው አቶ መሀመድ ኑር ችግሩ በጊዜ መፍትሔ ካልተፈለገለት በቀጣይ ሌላ ችግር ይወልዳል ይላሉ። "ምክንያታቸው ያው በደም መመለስ ነው። በጣም የሚያሳዝን ነው። እንደው እልባት ቢያገኝ ምናልባት ይሄ የሰሜኑ ጦርነት አክትሞለት ምናልባት እንደው መፍትሔ ይገኝ ብለን እንጠብቃለን እንጂ በጣም ሰው አለቀ በዚህ ምክንያት። በተደጋጋሚ እየሞተ ነው አሁን በዚህ በእኛም አሁን በጣም በቋፍ ላይ ነው በጣም አሁንም አስቸጋሪ ነው አሁን። " በአማራ እና አፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችን ለማስቀረት ምን እየተሰራ እንደሆነ በአማራ ክልል የሀብሩ ወረዳ፣ በአፋር ክልል የእዋ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ጋር ስልክ በመደወል እና መልእክት በመላክ ሀሳባቸውን ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ኢሳያስ ገላዉ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ