“ለውጥ እናመጣለን ብለን” ኢትዮጵያን “ወደ ነውጥ ከተትናት” ፦ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
ዓርብ፣ የካቲት 28 2017
ዐቢይ አሕመድን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያበቃው የኢትዮጵያ የለውጥ እንቅስቃሴ በተጋጋለበት ወቅት ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ውስጥ በተራማጅነት ይጠቀሱ ከነበሩ ፖለቲከኞች አንዱ የሆኑት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ካዋለዱት ብልጽግና ፓርቲ ተለያይተው ኑሯቸውን በውጪ ሀገር አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ለገባችበት የፖለቲካ ምስቅልቅል በሥልጣን ላይ የሚገኘውን መንግሥት አምርረው የሚኮንኑት ገዱ ከለውጡ በኋላ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደሕንነት አማካሪ ሆነው የሠሩ ሲሆን በስተመጨረሻ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነበሩ።
ገዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ እና መንግሥት በዋናነት ያቃቃራቸው በአማራ ክልል በመካሔድ ላይ የሚገኘው ግጭት ጉዳይ ነው። ግጭቱ “በአገዛዙ ታቅዶ አማራን ለማዳከም” የተቀሰቀሰ እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት ጉምቱው ፖለቲከኛ በድርድር ይፈታል የሚል አቋም የላቸውም።
አቶ አያሌው ጎበዜን በመተካት ከታኅሳስ 2006 እስከ የካቲት 2011 ድረስ ክልሉን ለአምስት ዓመታት በፕሬዝደንትነት የመሩት አቶ ገዱ ግጭቱ የሚገታው የኢትዮጵያ መንግሥት “እየሔድኩበት ያለው መንገድ አያዋጣም ብሎ ጦርነቱን ሲያቆመው” አሊያም “ሕዝቡ በፋኖ እየተመራ እያደረገ ያለው ትግል ተጠናክሮ በጉልበት አገዛዙ የሰላም አማራጭ እንዲቀበል በማድረግ ብቻ” እንደሆነ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ወደ ግጭት የገባው ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በቅጡ ሳያገግም ነው። የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ለብርቱ ሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ የዳረገውን ደም አፋሳሽ ጦርነት “ማስቀረት የሚቻል” እንደነበር ይናገራሉ።
ጦርነቱ በደቡብ አፍሪካ በተፈረመ ግጭት የማቆም ሥምምነት መገታቱን ያስታወሱት አቶ ገዱ “ያ አማራጭ በፊትም ነበረ” በማለት በብልጽግና ፓርቲ እና በህወሓት መካከል የተካረረው ልዩነት በድርድር የሚፈታበት ዕድል ቀድሞም እንደነበረ ጠቁመዋል።
“ያን ጦርነት ማስቀረት ባለመቻላችን እኔ በግሌ ከፍተኛ ሐዘን ነው የሚሰማኝ” የሚሉት የቀድሞው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣን “ታሪካዊ ስህተት” እንደሆነ ያምናሉ።
ጦርነቱ ግጭት በማቆም ሥምምነት ይገታ እንጂ ዳግም ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ከፍተኛ ሥጋት አለ። በተለይ የምዕራብ ትግራይ ወይም የወልቃይት እጣ-ፈንታ እስካሁን መፍትሔ አልተበጀለትም። አቶ ገዱ “በትግራይ እና በአማራ መካከል ያለው ልዩነት ከእንግዲህ በኋላ ሊፈታ የሚችለው ሰላማዊ በሆነ ንግግር ብቻ ነው” የሚል አቋም አላቸው።
በአሁኑ ወቅት መቀመጫቸውን በውጪ ሀገር ያደረጉት ጉምቱ ፖለቲከኛ በቅርቡ የተቋቋመው የአማራ ዓለም አቀፍ ትብብር ከፍተኛ አማካሪ ናቸው። ይህ ትብብር በውጪ ሀገራት የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ገዱ የአማራ ሕዝብ እያደረገ ነው ለሚሉት “ከፍተኛ የኅልውና ትግል” የሚያደርገውን ዕገዛ ለማስተባበር ያለመ ነው።
ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ-መጠይቅ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ